በገረሱ ቱፋ*
የእሬቻ በዓል በኦሮሞ ሕዝብ ከሚከበሩ በዓላት ቀዳሚውን ሥፍራ የሚይዝ በዓል ነው። በዓሉ የሚከበረው የክረምት ወቅት አልቆ የፀደይ ወቅት የሚጀምርበት ጊዜ ነው። የዝናብ፣ የጎረፍ እና የጨለማን ወቅት አሻግሮ ለፀደዩ ብርሃን ላዳረሰ አምላክ ምስጋና በማቅረብ ማለት ነው። በአሁኑ ጊዜ የእሬቻ በዓል በኦሮሚያ/ኢትዮጵያም ሆነ በአፍሪካ አህጉር በቀል ሆኖ በብዙ ሚሊዮኖች የሚከበር በህዝብ ቁጥር ተወዳዳር የለለው በዓል ነው። ይህ ማለት የእሬቻ በዓል ለኦሮሞም ብቻ ሣይሆን ለመላ ጥቁር አፍሪቃውያን ታላቅ በዓል ነው ማለት ይቻላል።
ለመሆኑ የእሬቻ በዓል እንዴት ተጀመረ? በምርቃት የሚከፍቱት እነማናቸው? የእሬቻ ጊዜ እንዴት ይወሰናል? የእሬቻ በዓል ሃይማኖታዊ ነው ወይስ በህላዊ? ለኦሮሞ ህዝብ ብሄራዊ አንድነት ያለው አንድምታ ምንድነው? የሚሉ ጥያቄዎችን በዚህ አጭር ጽሑፍ ለመመለስ እሞክራለሁ።
የእሬቻ በዓል ታሪካዊ አመጣጥ
የእሬቻ በዓል እንዴት እንደ ተጀመረ የሚገልፅ ጥልቅ ጥናት የለም። አከባበሩም ከቦታ ቦታ ውሱን ልዩነቶች ይኖሩታል። የኦሮሞ ህዝብ ለረጅም አመታት ታሪካዊ እና ባህላዊ ክንዋኔዎቹን በህዝባዊ ትውስታ መልክ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲያስተላለፍ ስለነበረ፤ ሰፊና ጥልቅ ጥናት ቢደረግ ታሪካዊ አመጣጡን በተሻለ ሊያስረዳ የሚችል በቂ መረጃ ሊገኝ እንደሚችል ምንም ጥርጥር የለም። ለጊዜው በቱለማ ኦሮሞ አፈ ታሪክ ላይ ተንተርሼ የተወስነ ፊንጭ የሚሰጡ ነገሮችን ለማሳየት እሞክራለው።
በቱለማ ኦሮሞ ትውፊት እንደሚነገረው የእሬቻ በዓል የተጀመረው የገዳን ሥርዓት ለማደስ ከ226 ገዳዎች ወይም ከ1800 አመታት በፊት ከመደ-ወላቡ ተነስቶ በመጣው ናቤ ነው። በቱለማ ትውፊት መሠረት ናቤ ስሪያ አንስታ ያመለጥች ግደሩን ተከትሎ ለዘጠኝ ወራት ከተጎዘ በኋላ በሆራ ሐረሰዲ ያገኛታል። ጊደሩን ሲያገኛት ልትወልድ የደረሰች በመሆኑ፣ “ኦዳ ነቤ ስትደርስ ለመወለድ ውሃ ፈሰሳት” ይላል የቱለማ ኦሮሞ ትውፊት።
በመቀጠልም ጨፌ ደንጏራ በሚባለው ቦታ ወለደች። ጨፌ ቱማ የሚባለው ቦታ ደግሞ “የእንግዴ ልጁዋ ወጣ” ይላል ቱውፊቱ። ናቤም የተወለደው ኮርማ እስኪያደግ ድረስ ጠብቆ ይዞ ወደ መጣበት መደ ወላቡ ለመመለስ አስቦ ነበረ። ይሁን እንጂ፣ ኮርማው የረር ተራራ ላይ በመውጣት እምቢ ይለዋል። ከዚያ በሁዋላ ወደ መደ ወላቡ በመመለስ የተቀሩ ወገኖቹን ይዞ ይመለሳል። ይላል አፈታሪኩ። በዚህ የተነሳ በቱለማ ኦሮሞ ምርቃት ዉስጥ “የረር ኮርማ” የሚለው ሃረግ ምንጊዜም አይቀርም። ናቤ የቱለማን ገዳ ባዲስ መልክ እንዳዋቀርና በአከባቢው የተለያዩ ቦታዎች ሲዘዋወር እንደነበረ ይነገራል። በአካባቢው በቆየበት ጊዜ እሱ የተዘዋወረባቸው ቦታዎች፣ የተሸገራቸው መልካዎች፣ ያረፈባቸው ጥላዎች እና የወጣባቸው ተራራዎች ከሞላ ጎደል በቱለማ ምርቃት ውስጥ ይንፀባረቃሉ። ስለዚህ የቱለማ ሰዎች እነዛን እሱ የተሻገራቸውን መልካዎች ሲሻገሩ፣ ጥላዎች ሲያልፉ ወይም ተራራዎችን ሲወጡ እሬቻ ያደረጋሉ።
የቱለማ ኦሮሞ የገዳ ጉባዔ በኦዳ ናቤ ሲያካሂዱም፣ ወደ ጨፌ የሚጓዙ የቱለማ ሃዩ (አንጋፋ) እና አባ ፋጂም የሚሄዱበት መንገድ ናቤ በአካባቢው በቆየበት ጊዜ ተጉዞባቸዋል ተብለው በሚታመኑ መንገዶች እንጂ ዝም ብለው ከቤት ተነስተው ባገኙት መንገድ አይጓዙም።
እነዚህ በአብዛኛው በቱለማ ኦሮሞ ምርቃት የሚንፀባረቁ ቦታዎች ከሞላ ጎደል የሚከተሉት ናቸው። ሆራ ሃረሰዲ፣ ኦዳ ናቤ፣ ጨፌ ዶንጏራ፣ ጨፌ ቱማ፣ ሆራ ፊንፊኔ፣ ዸካ ዐራራ፣ ብርብረሣ ፎቃ፣ የረር ኮርማ፣ ቱሉ ጩቋላ እና መልካ አዋስን መጥቀስ ይቻላል። እሬቻ ማለት ጥሬ ትርጉሙ ለተከበረ ወይም ለተቀደሰ ነገር የሚከፈል ዋጋ ማለት ነው። ለምሳሌ የባህል መድሃኒት ለሚሰጡ ሰዎች ወይም ልጆችን ለማሰመረቅ (ammachiisaa) ቃሉ ጋር ሲወሰዱ፣ ገንዝብ ወይ ሳር ይሰጣል። ያ እሬቻ ይባላል። “እሬቻ” የሚለው ቃል ቀጥተኛ ትርጉሙ “ዋጋ” ማለት ነው። ሳር ደግሞ እርጥበቱ ህይወትን የሚያሳይ በኦሮሞ ባህል ከፍተኛ ክብር የሚሰጠው ነገር ነው። በዚህ የተነሣ የክረምትን ጨለማ በሰላም አሻግሮ ወደ ፀደይ ወቅት ላደረሰ አምላክ በምስጋና መልክ የሚቀርብ ስጦታ ነው። እሬቻ የምስጋና ቀን ነው የሚባለው ለዚህ ነው።
የእሬቻ ምርቃት እና ዜማዎች፡
ኦሮሞች ለእሬቻ ወደ መልካ በሚጓዙበት ጊዜ የሚያዜሙት “ማሬ-ሆ” (Maree Hoo) ይባላል። መሬ-ሆ ወደ መልካ ስኬድ ሁል ጊዜ የሚዜም ዜማ ነው። መልካ ማለት አንድን ወንዝ በቀላሉ ልሻገሩ የሚችሉበት ቦታ ማለት ነው። ወንዝን ከጥልቀቱ ወይም በውስጡ በሚገኙ አደገኛ እንስሣት የተነሣ በሁሉ ቦታ መሻገር፣ ውሃ መቅዳት፣ መጠጣት፣ ወይም ከብቶችን ማጠጣት አይቻልም። እነዚህን ሁሉ ማድረግ የሚቻልበት አደገኛ ያልሆነ የወንዝ ወይም የሐይቅ ቦታ መልካ ይባላል። መልካዎች የየራሣቸው ስሞች አላቸው።
የእሬቻን ምርቃት በተመለከተ ከላይ ለመግለፅ እንደሞከርኩት፣ ከአካባቢ ወደ አካባቢ መጠነኛ ልዩነት ይኖረዋል። በዚህ ጽሁፍ በቱለማ ኦሮሞ የምርቃት ሥረዓት ምን እንደሚመሥል ለማሳየት እሞክራለው። መልካው አጠገብ ሰው እንደ ተሰበሰበ የአካባቢው የዕድሜ ባለፀጋ ታላቅ የሆነ ሰው ለምርቃት ይጋብዛል። በቱለማ ኦሮሞ ታላቅነት በሶስት መመዘኛ ይወሰናል። አንደኛው እና ታላቅ የሚባለው በወቅቱ ሥልጣን ላይ ያለው ገዳ አባል የሆነ ሰው እንደ ታላቅ ይወሰዳል። ለምሳሌ በአሁኑ ወቅት ሥልጣን ላይ ያለው የቱለማ ገዳ ቤልበያ/ሆረታ ይባላል። አንዳንድ ሰዎች ሜልባ ይሉታል። ‘ቤልባያ/ሆረታ አለ?’ ተብሎ ሲጠየቅ፣ ካለ አቤት ይላል፤ ከለሌ ደግሞ የለም አይሉም ገልማ ነው ያለው (Galma Jira) ይላሉ። ገልማ የተቀደሰ ቦታ ማለት ነው። ቀጥለው ደግሞ ከሶስቱ የቱለማ ልጆች (ዳጪ፣ በቾ እና ጂሌ) ውስጥ ታላቅ የሆነው ዳጪ አለ? ተብሎ ይጠየቃል። ከለ ወደ ምቀጥለው ይከዳል። ካለሌ ደግሞ ገልማ ነው ያለው ተብሎ ይታለፋል። ቀጥሎም፣ ከዳጪ ሶስት ልጆች (ገላን፣ ኦቦ እና ሶዶ) ታላቅ የሆንው፣ ገላን አለ? ተብሎ ይጠየቃል ካለ ወደ 6ቱ የገላን ልጆች (ጂዳ፣ ሊባን፣ አደዓ፣ ጋዱላ፣ ኣቡ እና ወረጃርሣ) ይሄዳሉ፤ ገላን ከለሌ ግን ኦቦ አለ ተብሎ ቀጥሎ ወደ አለው ንዑስ ጎሣ ይከዳል። ከዚያም፣ ከስድስቱ ገላን ውስጥ ጅዳ አለ ተብሎ ይጠየቃል፤ ጅዳ ካለ አምስት ልጆች ስለ አሉት ኩራ አለ የምል ይቀጥላል በዚህ መልክ እስከ መጨረሻው ከሄዱ በኃላ፤ በዛ ቦታ የሚገኝ ታላቅ ይለያል። ከአንድ በላይ ሰዎች የአንድ ገዳ አባሎች እና የአንድ ንዑስ ጎሣ ተወላጆች ከተገኙ በዕድሜ ታላቅ የሆነ ሰው መድረኩን ወሰዶ ምርቃቱን ይቀጥላል። እዛ የተገኘው ሰው በጣም ልጅ ከሆነ “ሆፎሊ” (Hoffal) ብሎ በዕድሜ ታላቁ ለሆነ ሰው ማሰተላለፍ ይችላል። የተቀበለውም ሽማግሌ ህዝቡን “Na Hoffalchaa” ብሎ እንደገና ፍቃድ በመጠየቅ ምርቃቱን ይቀጥላል።
የእሬቻ በዓል ጊዜ አወሳስን
የበዓሉ ጊዜ የሚወሰነው የአሁኑ አይነት የቀን አቆጣጠር ከመምጣቱ በፊት አያንቱ (ayyaantuu) በሚባሉ በህላዊ ኮከብ ተመራማሪዎች (አስትሮኖመሮች) ነው። በኦሮሞ ባህል ከጥንት ዘመናት ጀምሮ የጨረቃንና የከዋክብትን እንቅስቃሴ በማቀናጀት የአመታትንና የወቅቶችን ለውጥ መወሰን እጅግ በጣም የቆዬ ባህል መሆኑ በጥናትም ጭምር የተረጋገጠ ሃቅ ነው። ታዋቂው የአንትርፖሎጅ እና የገዳ ሥርዓት ተመራማሪ ፕሮፈሰር አስመሮም ለገሰ የአሜሪካን የህዋ ምርምር ሳይንቲስቶችን በመጨመር እንዳረጋገጡት የኦሮሞ ህዝብ የብዙ ሺህ አመታት የኮከብ ምርምር (Dhahaa) ወይም አስትሮኖሚ ባህል ነበረው። በዚሁ መሰረት አያንቱዎች የኮኮቦችን እንቅስቃሴ በመከተል የእሬቻን ትክክለኛ ቀን ይወስናሎ።
እንደሚታወቀው መስከረም 21 ፀሓይ የምድር ወገብ ላይ የምትሆንበት ወይም በእንግሊዝኛው equinox የሚባለው ጊዜ ነው። ይህ ቀን ቀንና ለልት በትክክል እኩል የምሆንበት ጊዜ ነው። በተጨማርም ይህ ጊዜ በትክክል ወቅት አስትሮኖሚካሊ የሚቀየርበት እና አዲስ የፀደይ ወራት የሚጀምርበት ጊዜ ነው። በአሁኑ ጊዜ በአካባቢው የኦርቶዶክስ ሃይማኖት እና የጁላያን ካሌንደር ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ በህላዊው እና በይዘቱ በጣም ሣይንሣዊ የሆነው የኦሮሞ የቀን አቆጣጠር በመዳከሙ፣ ጊዜው ከመሰከረም 19 እስከ 24 ባለው እሁድ ላይ ይከበራል። የወቅት ለውጥ ሲደረግ በስፋት ከሚደረገው የሆራ ሃርሰዲ እሬቻ በፊት የሚከበሩ ሌሎች በዓሎች አሉ። እንደ ደመራ (Ibsaa Oromo) ማብራት፣ ደመራ በበራ በንጋታው ሌሊት ከብቶችን ከዛ በፊት ግጠው ወደ ማያውቁበት ከሎ ወስዶ ማስጋጥ ወይም የዋሬ (Waaree) በዓል፣ ከነጋ በኃላ ደመራ በበራበት ቦታ የቤተሰብ እሬቻ ማድረግ፣ ቡና አፍልቶ አዲስ የደረሰ የበቆሎ እሼት፣ የአተርና ባቄላ መብላት የመሳሰሉትን ይጨምራል። ማታም ለመጀመሪያ ጊዜ የወለዱ ላሞች ወተታቸው ተራቅሞ ግማሹ ቅቤ ተደረጎ ቅንጬ በመስራት እና ወተቱን መጠጣት የኦኮሌ ስርዓት (sirna Okolee) የሚባል ሥርዓት ይጨምራል። ጊዜው ከመስቀል በዓል ጋር ከመቀራረቡ ጋር ተያይዞ አንዳንድ ሰዎች የክርስትና ሃይማኖት ቅጥያ አድርገው ያዩታል። ይህ አይነት ግንዛቤ ፍፁም ስህተት ነው። የክርስትና ሃይማኖት ከመጣ በኃላ ጊዜው አንድ ላይ እንዲገጣጠም ስለ ተደረገ ሁኔታው ብዥታ ለመፈጠር ችሎዋል። እንደዚህ አይነቱ ብዥታ በኦሮሞ ብቻ ሣይሆን በአውሮፓም ጭምር ገጥሞዋል። አሁን እንደ ክርስትያን የምናቃቸው የእስተር፣ የክርስማስ እና የአዲስ አመት በዓላት ሌላ ይዘት የነበራቸው ቅድመ ክርስትያን የሮማውያን ሀገር በቀል በዓላት ነበሩ። ይሁን እንጅ በ380 አ/ም የክርስትና ሃይማኖት መንግስታዊ የሮማውያን ሃይማኖት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ቅድመ ክርሥትያኖችን ባህሎችና በዓሎች ከክርስትና ሃይማኖት በዓሎች ጋር ተደባልቀዋል፣ በክርስትና ተተክዋል ወይ ወደ ክርስትና ተቀይረዋል። በኦሮሞ ዘንድም የገጠመው ተመሣሣይ ሁኔታ ነው። ይህንን ለማረጋገጥ የመሰቀል በዓል በሚከበርበት ጊዜ የሚፈፀሙ ሥርዓቶች እና የሚዘፈኑ ባህላዊ የኦሮምኛ ዘፈኖችን ማየት ይቻላል። ምንም አይነት ክርስተያናዊ ይዘት የላቸውም።
የእሬቻ በዓል ባህል ነው ወይስ ሃይማኖት?
የእሬቻ በዓል ሃይማኖት ወይስ ባህል ነው የሚለው ጥያቄ ተደጋግሞ የሚነሣ ጥያቄ ነው። በርግጥ በሃይማኖት እና ባህል መካከል ያለው ድንበር በጣም ቀጭን ነው። በዓለም ላይ ያሉ ብዙ በዓሎች በአንድ ወቅት ሃይማኖታዊ መስረት ነበራቸው። የፈረንጆቹን አዲስ አመት ብንወሰድ ቅደመ ክርስትያን እና ድህረ ክርስትያን ሃይማኖታዊ ይዘት ነበረው። ይሁን እንጂ በአሁኑ ወቅት፣ ክርስትያኖች፣ ሙስሎሞች፣ ይሁዳውያን፣ ሂንዱዎች፣ ቡድስቶች፣ ኮንፍሸውያንና የጃፓኖቹ ሽንቶዎች እንደራሳቸው በዓል ወሰደው በባህላዊው መልክ የፈረንጆቹን አዲስ አመት በድምቀት ያከብራሉ።
በተመሣሣይ መልኩ በአብዛኛው የእስልምና ሃይማኖትን የሚከተሉ ኢራኖች ሃይማኖታዊ መሠረት የነበረውን እና አሁንም የጥንታውያን ፋርሲዎች ወይም አራያኆች ሃይማኖት የሆነውን የዞራስተራያውኖችን አዲስ አመት ናውሩዝን (Nawruz) በፍተኛ ድምቀት ያከብራሉ። ናውሩዝ ለፉርሲ ሺዓ ሙስሊሞች፣ ለአረብ ሱኒ ሙስሊሞች፣ ለአርማይክውያን፣ አሲርያንና ለከላዳውያንን ክርስትያኖች፣ ለሚዝረሃ ሃይሁዶች፣ ለአሪያን ዞራስተሮች፣ ለየዘዲ ኩርዶች እንዲሁም ለአዛሪ እና ባሉቺ ሙስሊሞች የሁሉም ኢራናውያን የጋራ አዲስ አመት እና በህላዊ በዓል በመሆን በጋራ በድምቀት ይከበራል። የሚገርመው ይህ በዓል የሚከበረው ከእሬቻ ስድስት ወራት በሁዋላ ጸሃይ እንደገና በምድር ወገብ ላይ በምትሆንበት ጊዜ March 21 ነው። የእሬቻ በዓል የሚከበረው የደቡባዊው ንፍቀ ክበብ ተገባዶ የፀደይ ወራት በሚጀምሩበት ጊዜ ስሆን የፋርስው ናውሩዝ ደግሞ የሰመናዊው ንፍቀ ክበብ አልቆ የፀደይ ወራት ስገቡ ነው።
በተመሣሣይ መልኩ የኦሮሞ ህዝብ የደረሰበትን ረጅም የባህል ወራራ ተቋቁሞ፤ ከተረፉለት ባህሎች፣ የእሬቻ በዓል ከፍተኛ ስፍራ የሚይዝ ነው። ስለዚህ ኦሮሞዎች ምንም ዓይነት ሃይማኖት ቢከተሉ የእሬቻ በዓል ሁሉንም ኦሮሞዎች የሚያስተሳስር ባህላዊ እሴታቸው ነው። በአሁኑ ጊዜ በየአመቱ ቢያንስ ከሁለት እሰከ ሶስት ሚሊዮን ኦሮሞዎች ወደ ቢሾፍቱ በመሄድ በኦሮሞ ብሔራዊ የእሬቻ ክብረ በዓል ላይ ይሣተፉሉ። ይህ ማለት ከአጠቃላዩ የኦሮሞ ህዝብ 10% የሚሆነው ህዝብ በአካል እና በቀጥታ ይገናኛል ማለት ነው። በየአመቱ ከአጠቃላዩ ህዝብ አስር ፐርሰንቱ መገናኘት ማለት ለኦሮሞ ህዝብ ብሔራዊ ትሥሥር እና እድገት ከፍተኛ አሰተዋጾ አለው። ከዚህም በተጨማሪ ይህን መጣጥፍ ስጀምር እንደገለፅኩት የእሬቻ በዓል በብዙ ህዝብ የሚከበር ብቸኛ አህጉር በቀል የሆነ በዓል ነው። ይህ ደግሞ ወደፊት የቱሪስት መስህብ በመሆን የኦሮሞ ህዝብን ለዓለም ህዝብ የበለጠ ለማስተዋወቅ ያግዛል። በዚህ ላይ በሀገር ውስጥ እና ውጭ ሀገራት ውስጥ የሚኖሩ የኦሮሞ ሙሁራንና አክቲቭስቶች በዓሉ በዩኔስኮ አለም አቀፍ ቅርስነት እንዲመዘገብ ጥረት እንዲያደርጉ ለማስታወስ እፈልጋለው።
መልካም የ2014 የእሬቻ በዓል!
* ገረሱ ቱፋ: geresu@gmail.com
=>gadaa