Monday, October 20, 2014

ከማይሰለጥነዉ የዕብሪተኞች አንደበት: “እስርቤቱ ኦሮሞ ኦሮሞ ይሸታል…”

ከማይሰለጥነዉ የዕብሪተኞች አንደበት: “እስርቤቱ  ኦሮሞ ኦሮሞ ይሸታል…”


by Jiituu Lammii | October 20, 2014
ዘመነ ቅኝ-ግዛት (the colonial era) ሲታሰብ ለኣፍርካ ሕዝብና ለምድሪቷ የማይሽር  መራራ ትዝታ ኣለዉ። የዚህ ክፉ ቀን የክፋቱ ልክ፣ የሕመሙ መጠንና የጸጸቱ ጥልቀት ከወሰን ያለፋ ዘመን ተሻጋሪ ነዉ።  የሀገር ባለቤትነትን ከመነጠቅ ኣልፎ ከሰብዓዊ ፍጡር ምድብ እስከ መዉረድ የደረሰ በደል የተስተናገደበት የታሪክ ጥቀርሻ በመሆኑ መቼም በጊዜ ወሰን የማይገደብ የታሪክ ትዉስታ ይዞ ይቆያል። ጥቁሩ ባለሀገር ሕዝብ (the indigenous people) በነጮቹ ወራሪዎች ዕይታ ሲመዘን እንደሳይጠን፣ ያልሰለጠነና ክፉ እንስሳ እንጂ እንደሰብዓዊ ፍጡር አይታሰብም ነበር። ይህንኑ አመለካከት ለማስረጽ ሲባልም ሁለንተናዊ ማንነቱን የሚያጥላሉ በርካታ አዋራጅ (pejorative) ስያሜዎች ተሰጥቶታል። የኣፍርካ ምድርም ቢሆን ወርቅና አልማዝ በገፍ እየታፈሰበት እንኳ የጨለማ ዕምብርት (heart of the darkness, the abode of barbarism and cruelty) ከመባል ኣላመለጠም።

በኣንጻሩ ደግሞ ነጮቹ ቅኝ ገዥዎች ለራሳቸዉ የሚሰጡት ግምትና ሁለንታናዊ ማንነታቸዉን የሚስሉት በታቃራኒዉ ገጽታ ነበር። ቋንቋቸዉ፣ ባሕላቸዉ፣ የተፈጥሮ ገፀ-ቀላማቸዉና ተክለ- ሰዉነታቸዉ በአጠቃላይ ሁለንተናዊ ማንነታቸዉ የመጠቀና የበላይ (superior) እንደሆነ ይሰብካሉ። ጥቁሩ ሕዝብ በኣእምሮ ብስለትም ሆነ በሰዉነት ብቃቱ የበታች (inferior) ሆኖ እንደተፈጠረ በጭፍኑ ይመሰክራሉ።  እንግሊዛዊዉ ታዋቂ ደራሲና ገጣሚ Rudyard Kipling ጥቁር ሕዝቦችን ማሰልጠንና ማስተዳደር የነጮቹ ዋነኛ ኃላፊነትና ሸክም እንደሆነ በድፍረት ተናግሯል። የብሪትሽ ቅኝ ግዛትን ወደ ኣፍርካ በማስፋፋቱ ሂደት ላይ ከፍተኛ ሚና የነበረዉ ፌረድሪክ ሉጋርድም (Frederick Lugard) በበኩሉ “ለዚህ ስልጣኔ ኣልባና የጭለማ ዕምብሪት ለሆነዉ ሕዝብና ምድር የባሕል ግስጋሴና የስልጣኔ ብርሃን ማምጣት ነዉ” በማለት የወረሪዎቹን ስዉር ዓለማ ምክንያታዊ ለማስመሰል ጥሯል።

ይህንን ኣንዱን የበላይ ሌላዉን የበታች ማድረግን ዓላማዉ ያደረገ ኣድሎኣዊ የማንነት አሳሳል( Identity characterization) ለመተግበር ከፍተኛ የቋንቋ ምሁራንን (lexicographers, psycholinguists, editors) ወዘተ የመሳሰሉትን እንዳሳተፋ ይነገራል። ትርጉሙ ወይንም ቃላቶቹ የሚሸከሙት ምስል(connotation) ከእዉነተኛዉ ኣፍሪካዊ ማንነት ጋር ምንም ዓይነት ዝምድና ባይኖረዉም እንኳ በሂደት ግን የሥነ-ልቦና ተጽዕኖ ማሳደሩ አልቀረም። ዛሬም ቢሆን እነዚህ ሁለቱ ቀለማት በብዙዎቹ ኣእምሮ ዉስጥ የሚፈጥሩት ምስልና የሚወክሉት ቃላዊ ፍቺ የተጽዕኖዉን ጥልቀት ያመላክታል። ያም ሆኖ ግን የሕዝቦችን እዉነተኛ ማንነት ዉጦ የሚቀር ኃይል አልተገኘምና ቀኑ ሲደርስ የጭለማ ስብከት በእዉነተኛ ብርሃን ከመሸነፍ አልተረፈም።

ለመንደርደሪያ ያህል ካነሳሁት አጭር ቅኝት ሰሞኑን በእጅጉ ሲከነክነኝ ወደ ሰነበተዉ ተመሳሳይ ጉዳይ ልዝለቅ። የኦሮሞን ሕዝብ ባህል፣ ቋንቋ፣ ታሪክና አጠቃላይ የማንነት እሴቶቹን ለመደምሰስ ዘመናትን ያስቆጠረ ዘመቻ ሲካሄድ መቆየቱ አጠያያቂ አይደለም። ሆኖም ግን ህዝቡ በዚህ ረገድ ባካሄደዉ ትግል በሚያስደንቅ ፍጥነት እዉነተኛ ማንነቱን በትዉልዱ ልብ ዉስጥ መልሶ ለመስረጽ ተችሏል። በዚህ የትግል ዕምርታ የሚደነግጡ ቀናተኛ ግለሰቦች ኣለዋቂነታቸዉን በሚያሳብቅ መልኩ በደነገጡ ቁጥር ኣላዋቂነታቸዉን የሚያጎላ አጸያፊ ቋንቋን ከመጠቀም ኣልታቀቡም።

‘ESAT Radio’ የሚባል ሚዲያ ሠሞኑን (ማክሰኞ፣ መስከረም 30 ቀን 2014ዓም) ባሰራጨዉ ዝግጅት ላይ የቀረቡት አቶ  ግርማ ታፈሳ የተባሉ ሰዉ በኦሮሞ ሕዝብ ላይ እየተካሄደ ያለዉን ስቃይ “እስር ቤቱ ኦሮሞ ኦሮሞ ይሸታል።” ብለዉ ሲያፌዙ ተደምጠዋል። ከዚህ በፊት ዶ/ር ብርሃኑ በዚሁ ሚዲያ (ESAT TV) ቀርበዉ ይህንኑ ጸያፍ ንግግር ሲጠቀሙ ተደምጠዋል። ይህ ከኣንዴም ሁለቴ ተደጋግሞ የተደመጠው ነዉረኛ ንግግር(filthy language) በኦሮሞ ህዝብ ላይ እየደረሰ ያለዉን የእስራት መጠን ለመግለጽ ነዉ ብሎ መቀበል የዋህነት ነዉ። ያንን ለመግለፅ ፈልገዉ ቢሆን ኖሮማ ከዚህ የተሻለ ገላጭ ቋንቋ ባልጠፋቸዉ ነበር። ይልቁንም ከዚህ በፊት የለመዱትን ለኦሮሞ ህዝብ ያላቸውን ንቀት ለመግለጽ የተጠቀሙበት አሽሙር እንጂ። ለነገሩማ የኦሮሞ ችግር ጉዳያቸዉ እንዳልሆነ እሙን ነዉ። ኦሮሞም ቢሆን ለጉዳዩ የነሱን ጥብቅና አይሻም።

የንግግሩን ምጸታዊ ፍቺ ለመረዳት ደብተራ መሆን አሊያም የዋሸራ ቅኔ ጠቢብነትን የሚጠይቅ አይመስለኝም። እርግጥ ነዉ ዛሬ በሚስጢራዊና ገሃዳዊ የማሰቃያ እስርቤቶች ዉስጥ የኦሮሞ ሕዝብ የስቃይ ሰለባ ሆኗል። እነዚህ እስርቤቶች በእስረኛ ብዛት ከመጣበባቸዉ የተነሳ በዉስጣቸዉ ያለዉ የንጽሕና አያያዝ ከግምት በላይ ኣሳሳቢ ነዉ።  የኣእምሮ ታማሚዎች ጭምር የሚታጎሩበት መሆኑ ደግሞ ጉዳዩን ይበልጥ አሳሳቢ ያደርገዋል። ቀን ቀን ከሰዉ ገላ ላይ የሚወጣዉ ላብና ትንፋሽ ከሚፈጥረዉ መጥፎ ጠረን ጋር እስኪላመዱ ድረስ መፈታተኑ አይቀርም። ቀን በሙቀት ሃይል የሚፈጠረዉ የሰዉ ላብ በታመቀዉ የቆርቆሮ ጣሪያ ላይ ተጠራቅሞ ሌሊት እንደዝናብ መልሶ ሲንጠባጠብ ማየት የተለመደ ክስተት ነዉ። የእስር ቤቱ ኣስከፊነት በዚህ ብቻ አያበቃም።
ታምመዉ ሕክምና ተከልክለዉ የሚሞቱ ወገኖቼ ቁጥር ቀላል አይደለም። በሕክምና ሰበብ መርዛማ መርፌ ተወግተዉ የተገደሉ፣ ለአካል ጉዳት የተዳረጉና የዘር ሕዋሳቸዉ እንዲመክን የተደረጉ ስለመኖራቸዉ የጊዜ ጉዳይ ሆኖ ነዉ እንጂ ከበቂ በላይ መረጃ ኣለ።
የነጻነት በሮች በነጻ አይከፈቱምና የኦሮሞ ህዝብ ከዚህ የበለጠ ዋጋም ቢሆን ለመክፈል ብቁ የሥነልቦና ዝግጅት አለዉ። እላይ የተገለጸዉን ጸያፍ ንግግር በማንኣለብኝነት ለመጀመሪያ ጊዜ ሲጠቀሙ የሰማኋቸዉ ሰዉዬ (ዶ/ር ብርሃኑ) አንድ ወቅት ላይ ዕድል ደርሷቸዉ ይህንን የእስርቤት ሁኔታ በመጠኑም ቢሆን አይተውታል።  ለዚህም ነዉ ይህንን አገላለጽ የመረጡት፣ በእዉን ይህንኑ አስከፊ የእስርቤት ሁኔታ ለመግለጽ ነዉ ብሎ መቀበሉ አስቸጋሪ የሚሆነዉ።

ሕዝብን መናቅ ኣላዋቂነት ነዉ። መዘዙም ቀላል አይሆንም። ከወራት በፊት አዛዉንቱ ፕ/ር መስፍን ለሚኒልክ የቀረበውን የዉዳሴ ዜማ የተቃወሙ ወገኖችን (ሲዳማዉን፣ ሶማሌዉን፣ ኦሮሞዉን፣ ሸካዉን፣ ወላይታዉን፣ መዠንግሩን) በአጠቃላይ የሚኒልክ ወረራ ሰለባ የሆኑ ሕዝቦችን  “የጨለማ ኃይሎች” ሲሉ ገልጸዋል። ለኣብነት ይህንን ኣነሳሁት እንጂ ዛሬ በየድረ-ገጹ ላይ የሚነበቡ የትንኮሳ ጽሑፎች ተበራክተዋል። ይህ ሃላፊነት በጎደለው መልኩ እንደዋዛ የሚወረወረዉ የንቀት ቃል እያደር ዋጋ ማስከፈሉ አይቀርም። ትላንት የተመላለሱበትን የተሳሳተ መንገድ ለዛሬ ጉዞም መመኘቱ ያለንበትን ነባራዊ ሁኔታ ካለመገንዘብ ይመነጫል። ከትላንት ስህተት ተምሮና ታርሞ ለመጪው መልካም ያለማሰብና ጭፍን የንቀትና የጥላቻ ጉዞ መሆኑን ያመላክታል። ፊጻሜዉም አደጋ አለዉ።

የማይሰለጥነዉ የዕብርተኞች አንደበት የመጨረሻ ዉድቀታቸዉን ያፋጥናልና – ሌተቀን ለሚያነቡላት ኢትዮጵያም ማምከኛ የሌለዉ ፈጣን ፈንጂ ማቀጣጠያ እያዘጋጁ ስለመሆኑ መገንዘብ ያሻል።

እንኳን ዘንቦብሽ ድሮም ጤዛ ነሽ  ይሉታል ይህ ነዉ።

ቸር ያሰማን!

ጂቱ ለሚ ነኝ


=>ayyaantuu

Oslo Peaceful Protesters Demand Freedom for Oromo Political Prisoners and Denounce Land-Grabbing in Oromiyaa (Oct. 16, 2014)

 
By Cameraman/Editor Oumer Ahmed:
By OroTV Oslo:

By OroTV Oslo:

Credits/Tags: , ,