Tuesday, June 10, 2014

አብዲ ብያ:- አዲሱን የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን የምንቃወምባቸዉ ምክንያቶች

አብዲ ብያ
የአዲስ አበባን ማስተር ፕላን የምንቃወመው፣
1. ህገ መንግስቱን ስለሚጥስ፡፡ ኦሮሚያ በፌዴራል አወቃቀር ሉዓላዊ ክልል ነው፡፡ መሬቱንም የሚያስተዳድረው ክልሉ ነው፡፡ አዲስ አበባ ደግሞ ተጠሪነቱ ለፌዴራል መንግስት ነው፡፡ ክልል በፌዳራል ስልጣን ውስጥ ጣልቃ አይገባም፣ ፌዴራል መንግስትም በክልል ጉዳይ ውስጥ ጣልቃ አይገባም፡፡
2. አዲስ አበባ በኦሮሚያ መሃል ስለምትገኝ፣ የተፈጥሮ ሃብት አጠቃቀምን፣ የአካባቢ ብክለትን በሚመለከት ለኦሮሚያ ልዩ ጥቅም ይጠበቅለታል የሚለው ህገ መንግስታዊ ድንጋጌ ከፀደቀ 20 ዓመታት ቢያልፈውም ተፈጻሚ ሊሆን አልቻለም፡፡
3. አሁን ሀገሪቱን እያስተዳደረ ያለው መንግስት መሬትን በመቀራመትና አርሶ አደሮችን ያለበቂ ካሳ ለመፈናቀል ተወዳዳሪ የማይገኝለት መንግስት በመሆኑ፣ የመሬት ስሪቱም መሬት የመንግስት ነው በሚል ታፔላ አርሶ አደሮችን ለማፈናቀል ወደ ኋላ ስለማይል ማስተር ፕላኑን መቃወም ተገቢ ነው፡፡ የኦሮሚያ መሬት እየተፈለገ ያለው ሁሉንም በእኩል በሚጠቅም ዘላቂ ልማት ሳይሆን በኪራይ ሰብሳቢነት መልክ የኢህአዴግ አባላትና ግብረ አባሮቹ መሬቱ ላይን ምንም ዕሴት ሳይጨምሩ የግል ሃብት ለማካበት አቋራጭ መንገድ ስለሆነ ሊፈቀድላቸው አይገባም፡፡
4. አዲስ አበባ/ፊንፊኔ ለኦሮሞ ህዝብ ታሪካዊ ከተማ እንደመሆኗ መጠን ለኦሮሚያ ክልል ህጋዊ ዋና ከተማ መሆን ሲገባው፣ በተግባር ኦሮሚያ አዲስ አበባ ቢሮ ከፍቶ ከመቀመጡ ውጭ ምንም የባለቤትነት መብት የለውም፡፡ አማራ ክልል፣ ደቡብ ክልል፣ ትግራይ ክልልና ሌሎቹም ብሄራዊ ክልሎች ዋና ከተማቸውን ለራሳቸው ያስተዳድራሉ፡፡ ኦሮሚያ የራሱን ዋና ከተማ ማስተዳደር ዕድል አላገኛም፡፡ በታሪክም ሆነ በጆኦግራፊ አቀማመጥ ከፊንፊኔ ውጭ ሌላ ከተማ ለኦሮሚያ ዋና ከተማነት አይታሰብም፡፡
5. የ125 ዓመታት የአዲስ አበባ ከተማ ዕድገት ጋር በተያያዘ ነባሩ የኦሮሞ ህዝብ ከከተማው ሲፈናቀል እንጂ በከተማው ዕድገትና ልማት ውስጥ ሲታቀፍ አልተመለከትንም፡፡ ይህ የሆነው ደግሞ በመሳሪያ ጦርነት ሳይሆን በባህልና ቋንቋ ጦርነት ነው፡፡ አዲስ አበባ ከተማ ከምኒልክ ጊዜ ጀምሮ ስታበረታተ የነበረው የአማርኛ ቋንቋ ተናጋሪ ባህልና ቋንቋን ነው፡፡ የባህልና ቋንቋ ተጽዕኖው ኦሮሞ ከአካባቢው እንዲሸሽ ያደርገዋል፡፡ ቋንቋና ባህል ማለት ድምጽ የሌለው መሳሪያ ማለት ነው፡፡ ቀላል ምሳሌ ልስጥህ፣ በአሁኑ ጊዜ አንድ ከጎጃም የመጠና አንድ ከሰበታ የመጠ የቀን ሰራተኛ በአንድ የግል ወይም የመንግስት ድርጅት አዲስ አበባ ውስጥ ተቀጥሮ በቀን ስራ ለመተዳደር የትኛው ዕድል ያለው ይመስለሃል? መቶ በመቶ የጎጃሙ ቀን ሰራተኛ የመቀጠር ዕድል ይኖረዋል፡፡ ምክንያቱም ባህልና ቋንቋ በሰው ልጅ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ከፍተኛ ተጽዕኖ አለው፡፡ ስለዚህ በፊንፊኔ ከተማ ውስጥ በነበሩት ኦሮሞዎች ላይ የደረሰው የዘር ማጽዳት ዘመቻ በሌሎች ኦሮሚያ አካባቢ አንዲደገም ስለማንፈቅድ ማስተር ፕላኑን ለመቃወም ከበቂ በላይ ምክንያታዊ ነን፡፡

No comments:

Post a Comment